
Photo: Andrew Heavens.
በዐይነ ህሊናው ወደኃሏ ለተጓዘ ሁሉ በስልሳዎቹ ዓመታት የነበረውን የወጣቱን የትግል እንቃስቃሴ ይቃኛል።ይህን ለማወቅ ከድርሳናት፣ አለዚያም ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ የእድሜ ባለጸጋ ከሆኑት መስማትና መረዳት ይቻላል። በዚያ ዘመን በተለያዩ ስያሜዎች በተደራጁ ድርጅቶች አማካኝነት ወጣቶች የትግል ሜዳውን ተቀላቀሉ። ጉልታዊ ሥርዐቱንና የብሔር ጭቆናን በመቃወም፣ እኩልነትን ለማስፈር በሚል መርሆች ህልቆ መሳፍርት የሚቆጠሩ ወጣቶች ፋኖ ተሰማራ አሉ። አንዳንዶች አብዮቱ ሲፈነዳ የጭቆና ማብቃያ ዘመን የተቃረበ መስሎዋቸው ነበር።
ትንሽ ሳይቆይ ወታደራዊ መንግሥት ስልጣን ጨበጠ። ወጣቱ ይበልጡኑ ጎራ ይዞ በአራቱም ማዕዘናት ትግሉ ተፋፋመ። ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ወጣቱ በየቀዬው፣ በየመንደሩ፣ በዱር በገደሉ እንደ ቅጠል ረገፈ። ወላድ እናት አጥብታ ያሳደገችው ልጅ በፊቷ የጥይት እራት ሆነ። አባት በመንገድ ላይ የልጁን እሬሳ በደም ተጨማልቆ አየ። ምሬቱን፣ ጩኸቱን፣ ልቁሶውን ወደ ፈጣሪው አሰማ። ከቤት ተጎትቶ ወጥቶ የጥይት እራት ሆነ። ጣእረ ሞት ምድሪቷን ሸፈነ። ለውጥ የተራበ የጥይት ማገዶ ሆነ። ወታደር፣ ጂፕ፣ ታንክ በየከተማው ተርመሰመሰ። ስንት ዋጋ ተከፎሎለት የተማረው ወጣት ጥይት በላው። ከየሆስፒታሉ እሬሳ እየወጣ በገንዘብ ተቸበቸበ። አይጣል!! ለዚያውም እሬሳን ለመግዛት የቻሉት ትንሽ የገንዘብ አቅም የነበራቸው ናቸው።እስራቱን፣ ግርፋቱን፣ ስደቱን ማን ቆጥሮት ይችላል። የእናቶች ለቅሶ፣ የአባቶች ሰቆቃ፣የዘመድ ኃዘን፣ የጥይት እሩምታ፣የሬሳ ጉድጓድ፣ የወገን ቅስም መሰበሩ ዛሬም ሊረሳኝ አልቻለም።እብሪተኛ ካድሬዎች፣ ጨካኝ የቀበሌ አባላት መረን የለቀቁ አብዮተኞች እንደነበሩ አይዘነጋኝም።ሌላው ቀርቶ የሕፃናት እሪታ፣ የታዳጊዎች ጩኹት ከዓይነ ህሊናዬ ገና አልጠፋም።የከበረ የሰው ሕይወት እንደ ቅጠል ረገፈ!!
ዛሬ ዛሬ ይህን የሰቆቃ ዘመን በአሉታ የሚተረኩትን ሳያይ ልቤ ያዝናል። ወጣቶቹ በእራሳቸው ጥፋት ያመጡት ነው እኮ በማለት ብይን የሚሰጡትን ስሰማና ሳነብ አወይ አለማወቅ እላለሁ። ወጣቱ ለውጥ ናፍቆት መስዋዕትነትን ከፈለ እንጂ ብርቀ ድርጊት አምሮት አልነበረም። ፍትሕ ተጓደለ፣ እኩልነት ጠፋ በማለት ለጥይት ተማገደ፤ በእስር ተንገላታ፤ ከአገር ተሰደደ። ታሪክን መናበብ የምንችለው በዘመኑ መነጽር ነው እንጂ በአዲሱ መነጽር ብቻ መሆን ባልተገባው ነበር። አዎ ያ ትውልድ ግራ ዘመም ይበዛዋል፤ ሶሻሊዝም የመፍትሔ መንገድ መስሎት ነበር። ከዚያ የሰቆቃ ዘመን የተረፈው ብዙኃኑ ወጣት፣ ከግራ ርዕዮተ ዓለም ተላቋል።ካሉም ለአገዛዝና ለጭቆና መሣሪያነት የተጠቀሙበት ብቻ ናቸው።
የወታደራዊ መንግሥት ቁንጮ የነበረው መንግሥቱ ኃይለማርያም የጻፋቸውን አንብቤ ይብሱኑ ጥላቻዬ ጨመረ። በአንጻራዊ አነጋገር እንደ መንግሥቱ “የታደለ” መሪ የለም። ከሥልጣን ቢወገድም በስደት አገር በመኖር በአገራችንን የሚከናወነውን ይከታተላል። በዚህ ሁሉ ዓመታት አንድም ቀን ስለ ሰራው በደል ተጸጽቶ አያውቅም። ይልቁንም “ዝንብ” እንኳ ገድሎ አለማወቁን ተናግሩዋል። በጽሑፉም የመጸጸት ምልክት አልታየበትም። አበስኩ ገበርኩ!!
አዲሱ ትውልድ ዛሬም ሰብአዊ መብት ይጠበቅ፣ አኩልነት ይሰፈን፣ ከመሬት ማፈናቀሉ ይብቃ፣ በጠቅላላው የዲሞክራሲ መብት ይጠበቅ በማለት ተጋድሎ በማድረግ ላይ ነው። ለዚህ ሞት፣ እስራት፣ ስደት፣ መሸማቀቅ ደርሶበታል። ሥርዐቱን ፊት ለፊ ገጥሟል። በተለይ የቄሮ ድርሳነ ትግል አስደናቂም፣ አስገራሚም ነው። የክብር ስፍራ ሊቸረው ይገባል።የገበሬውን መገፋትና መፈናቀል አይቶ ዝም አላለም። ሁኔታውን አሻፈረኝ በማለት በሰላማዊ መንገድ ያደረገው ታጋድሎ ጥልቅ ምዕራፍ ያሰጠዋል። የትግል ታክቲኩም አስገራሚ ነው። በአማራ ክልል የታየው የፋኖ እንቅስቃሴ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ግዛት ሲሸነሸን፣ መብት ሲረገጥ አይሆንም ብሏል። የመከራ ጽዋም በእጅጉ ደርሶበታል። የጉራጌ ዘርማም በድፍረት ይህን ሥርዐት ተጋፍጡዋል። በጠቅላላው ወጣቱ የከፈለው መስዋዕትነት ትልቅ ነው።
በአሁን ዘመን የተደረገውን የወጣቶች ትግል በአጭሩ ለመዘከር አይቻልም። በድሮው ወጣት ትውልድ ላይ የደረሰውን ሰቃይና መከራ ያየና የሰማ በዚህም ወጣት ትውልድ ላይ ይደገማል ብሎ የገመተ አይኖር ይሆናል። ይሁን እንጂ ተደገመ።ሲያሳዝን፣ ሲያናድድ!! ወጣቶች ሞቱ፣ ታሰሩ፣ ተገረፉ፣ ተሰደዱ፣ በብልታቸው ሳይቀር መስዋዕነትን ከፈሉ።ፍዳና ስቃይ ያደረሱበት ወገኖች ቢያንስ ይጸጸቱ ይሆን? ፍትሕ ከወዴት ይምጣ? አለዚያስ ታሪክ ይደገም ይሆን?
በአገራችን ከስድሳ ፐርሰንት በታች ያለው ሕዝብ በወጣነት ዕድሜ ክልል ውስጥ እንዳለ ይገመታል። ይህ ወጣት በሥራ አጥነት፣ በቤት እጦት፣ በደፈናው በኢኮኖሚ ችግር እንደሚሰቃይ ይታወቃል። ምንም እንኳ ወጣቱ የህብረተሰቡን ጥያቄዎችን አንግቦ የተነሳም ቢሆንም፣ የእራሱም ጥያቄዎች እንዳሉት ትልቅ ግምት ሊሰጠው ይገባል።እውነት ነው የህብረተሰቡ ችግር መፍትሔ ሲያገኝ የእርሱም አብሮ መልስ ያገኛል፤ ግን ልዩ ትኵረት አያስፈልገው ይሆን?
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ወጣቶች የጠየቁትን፣ ለዚህም የከፈሉት መስዋዕት መዘንጋት እንደሌለበት ለመጠቋቋም ነው።አሁን ለደረስንበት ውጤት ወጣቱ በሕይወቱ ጭምር መስዋዕትነት ከፍሏልና፣ መነጽራችን ወጣቱን የማየት ብቃት ሊኖረው ይገባል።
የወጣቱ ትግል መቼም አይዘነጋም!!
The post ምኞቴን አንድ ልበል… በትውልድ መነጽር (ገዙ በቀለ (ዶ/ር)) appeared first on Ethiopian News|Breaking News: Your right to know!.