ከአንተነህ መርዕድ ሃምሌ 2020 ዓ ም
በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1990 ዓ ም ህወሃቶች ጋዜጠኞችን በሙሉ ለቃቅመው ያሰሩበት ወቅት ነበር። ማዕከላዊ ሁላችንም ከክፍላችን እንዳንወጣ ተገድበን እያለ ሶስት አዲስ እስረኞች በበሩ ብቅ አሉ። እንግዳ ደሮ ይመስል ሰገግ ሰገግ እያሉ ግራ በመጋባትና በስጋት አካባቢውን ሲቃኙ እኛም በየክፍላችን ሁነን “እነማን ናቸው?” በሚል ጠያቂ ስሜት በዐይናችን እንፈትሻቸዋለን። ሞትም ቢመጣ ስሜታቸውን ከመግለጽ ወደኋላ የማይሉት የሱማሌ እስረኞች ሶማሌያዊ ገጽታ ያለውን እንግዳ በሩቁ ክፍላቸው ሆነው “ወርያ” እያሉ በጥያቄ ያጣድፉታል። ፖሊሶች ቢያስጠነቅቋቸውም ፍንክች አይሉም። ይሉኝታና ፍርሃት ከሸበበው አብዛኛው እስረኛ ይልቅ የሶማሌዎችን ድፍረት ምንጊዜም አደንቃለሁ። ከሶስቱ እስረኞች አንዱ ምዕራብ አፍሪካዊ ገጽታ አለው። ሶስተኛው ግን ከመርካቶ አካባቢ እቃ ሲያዞር ውይንም በስርቆት የተያዘ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው የሚመስለው።
ሶስቱንም በተለያየ ክፍል ሲደለድሏቸው ወጣቱ ኢትዮጵያዊ እኔ ካለሁበት ክፍል ተመድቦ ሲገባ አንዱንም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ አይችልም። እንግሊዘኛ ነው የሚናገረው። ሩዋንዳዊ ነኝ ሲል ማመን ተሳነን። መልኩ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ነበር የሚመስለው። ስሙን ስንጠይቀው “ዋልተንጉስ መኮንን” ብሎ ሲግረን ደግሞ የባሰ ግራ ተጋባን።
ታሪኩ ወዲህ ነው። ሶማልያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ አባቱ አቶ መኮንን ሩዋንዳ ሄደው አንዲት ቱትሲ ጋር ትዳር መስርተው ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ልጅ ወልደው ኪጋሊ ይኖራሉ። ዋልተንጉስ ከኪጋሊ ራቅ ካለችው ከተማ ኮሌጅ ገብቶ ሲማር የሩዋንዳ የዘር ፍጅት ይቀሰቀሳል። በሁለት ቀን ውስጥ ከተጨፈጨፉት ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ቱጺዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች የዋልተንጉስ አባት፣ እናትና ሁለቱ እህቶች ሰለባ ሲሆኑ እሱ እግሬ አውጪኝ ብሎ በሩጫ ኬኛ ገብቶ ተረፈ። ማመን የሚያቅተውን ሰው አምሳሉ የሆነ ሰውን በገጀራ ሲጨፈጭፍ ያየውና እድሜ ልኩን የሚያባነነው ዋልተንጉስ በዓለም ውስጥ የቀረው ቤተሰብ የለውም። በአንዲት ቅጽበት ህይወቱ እንዳልሆነ ሆኗል።
ብቸኛ የሆነች ህይወቱ ኬንያ ስደተኞች ካምፕ ሆኖ ሲጨልምበት አባቱ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ይነግረው ስለነበር ወደ ተስፋው ምድር ኢትዮጵያ መጥቶ የአባቱን ዘመዶች ፈልጎ በደቂቃ ያጣውን የማንነት ክር ሊቀጥል የአባቱ አገር ኢትዮጵያም እጇን ዘርግታ ልትቀበለው ተስፋ አድርጎ በመምጣት ደብረ ብርሃን አካባቢ የአባቱን ዘመዶች ሲያፈላልግ ባለስልጣናቱ ሃረጉን መፈለጉን ወንጀል አድርገው ሲኦል ወደሆነው ማዕከላዊ እስር ቤት ወረወሩት። ሃሳባችንን በነጻነት በመግለጻችን የታሰርነው ጋዜጠኞች ሆነ ፖለቲከኞች ማንነቱ ያስጠቃውን ዋልተንጉስን በምን አቅም ማጽናናት እንችላለን? የእሱን እስርና እንግልትስ እንዴት አድርገን ከዕኛው እናወዳድራለን?
ዓለም ቁጭ ብሎ ዐይኑ እያየ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ቱትሲዎች የተጨፈጨፉበት ሃያ ስድስተኛ ዓመት እየተከበረ፣ የሟቾቹ አጥንት ተሰብስቦ ለጎብኝዎች ክፍት ሆኖ ስለአለፈው ዘግናኝ ዘር ማጥፋት ውግዘት እየተሰማ ባለበት ወቅት ነው ዛሬ ኢትዮጵያውያን ዘራቸው፣ እምነታቸው፣ ጥረታቸው እየተለየ ስም ዝርዝራቸው ተይዞ ዘር ማጥፋት ተካሄዶባቸዋል። የትናንቱን አሿፊ ዓለምን እንተወውና እኛ ኢትዮጵያውያን ዐይናችንን ጨፍነናል። ጥቅምት ላይ የታረዱትን ኢትዮጵያውያን የዘር ማጥፋት ሰለባ መሆናቸውን ለማስተባበል ሟቾችን በጎሳ ከፋፍሎ ለማሳየት የተሞከረው ዛሬም በኦሮምያ ፖሊስ መግለጫ የሞቱት አብዛኞቹ ኦሮሞዎች ናቸው የሚል ትርጉም እንዲሰጠው የተሄደበት መንገድ አስተዛዛቢ ነው። አዎ “የሸዋ ኦሮሞዎች” ቱጺዎች ጋር እንደታረዱት እንደለዘብተኛ ሁቱዎች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። ታድያ ይህ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ወደ ቅዱስ ጦርነት ይቀይረዋል?
የሩዋንዳውን እልቂት አጀማመርና ፍጻሜ እናነጻጽረውና ፍርዱን ንጹህ ህሊና ላላቸው አንባቢያን እንተወው።
ሩዋንዳ ሁቱዎችና ቱትሲዎች የሚኖሩባት አገር ብቻ ሳትሆን ሁለቱ ጎሳዎች በቋንቋ ሆነ በእምነት የሚለያዩ አይደሉም። ሁቱን ከቱትሲ መለየት በጣም ያስቸግራል። እ ኤ አ 1935 ዓ ም ቅኝ ገዥዋ ቤልጀም ከፋፍላ ለመግዛት እንዲመቻት አብረው ለዘመናት የኖሩትን ቱትሲና ሁቱ በመታወቂያ እንዲለያዩ አደረገች። ህወሃትም ኢትዮጵያውያንን ከፋፍላ ለመግዛት ይህንኑ ነው ያደረገችው። መታወቂያ ላይ ብሄር ብሄረሰብ ማስፈርና ክልልን በዘር መሸንሸን።
የቱትሲና የሁቱ ልሂቃን የፖለቲካና የኤኮኖሚ የበላይነትን ለመያዝ በየዘራቸው ተቧድነው ልዩነቱን ማስፋቱን ተያያዙት። የእኛም በየጎጣቸው መንገስ የፈለጉ ልሂቃን ይህንኑ መንገድ ነው የተያያዙት።
የሁቱ ልሂቃን መገደል አለባቸው ያሏቸውን ቱትሲዎችና እንቅፋት ይሆኑናል ያሉዋቸውን ለዘብተኛ ሁቱዎችን ስም ዝርዝር ለቅመው ያዙ፣ ለወገኖቻቸውም ገጀራ ወይም ሜንጫ ከውጭ አስገብተው አስታጠቋቸው። እኛስ አገር አዲስ አበባንና ሌሎችን ከተሞች የሚያጠቁ፣ የሚያርዱ፣ የሚዘርፉ፣ የሚያቃጥሉ መንጋ ሜንጫ አስታጥቀው በመኪና እየጫኑ ከቦታ ቦታ አላሰማሩም?
ልዩነቱን ለማስፋት የሩዋንዳ ብሄራዊ ሬድዮ ጣብያው ስላልተመቻቸው “ሬዲዮ ቴሊቪዝዮን ሊብሬ ዴ ሚሌ ኮሊንስ” ወይንም (RTLMC) አቋቁመው ሌት ተቀን ጥላቻን ሰበኩ፣ የግደለው ትዕዛዝና ስምሪትም ሰጡ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ኦ ኤም ኤን፣ ድምጺ ወያኔ፣ የትግራይ ቲቪና ሌሎችም ሚድያዎች ሌት ተቀን ልዩነትን፣ የእልቂት ቅስቀሳንና ስምሪትን ሰበኩ።
የሩዋንዳው ፕሬዝደንት ጃቪናል ሃብያሪማና እንዲሁም የቡሩንዲው ፕሬዝደንት ሳይፕሪን ንትራያሚራ (ሁለቱም የሁቱ ጎሳ አባላት ናቸው) የተሳፈሩበት አውሮፕላን እ ኤ አ አፕሪል 6 ቀን 1994 ዓ ም በሚሳይል ተመትቶ ሁሉም ሞቱ። ይህንኑ አጋጣሚ ይጠባበቁ የነበሩ የሁቱ ልሂቃን በነጋታው የዘር ፍጅቱን ጀመሩትና በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሩዋንዳዊ ቱትሲና ለዘብተኛ ሁቱ ህጻን፣ ሽማግሌ፣ በሽተኛና ጤንኛ ሳይመርጡ ጨፈጨፏቸው።
በተመሳሳይ ሁኔታ ይህ ድርጊት ሩዋንዳ በተፈጸመ ሃያ ስድስተኛ ዓመት ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ ም ማታ በአዲስ አበባ ታዋቂውንና ተወዳጁን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል የእርስ በርስ እልቂት እንደተደገሰልን ይህን ያህል ሰው ታርዶ እንኳ ክህደት(ዲናያል) ውስጥ ያለነው ብዙ ነን። ህወሃቶችና የኦሮሞ ጽንፈኞች የሩዋንዳን ማስተር ፕላን (ብሉ ፕሪንት) ያለብዙ ልዩነት እንደተጠቀሙበት እውነቱ ፈጥጦ ይታያል። ከሃያሁለት ዓመት በፊት ጨለማ የዋጠውና የመጨረሻ ተስፋ ያደረጋት ኢትዮጵያ የካደችው ዋልተንጉስ መኮንን ህመም የተሰማኝ አሁን ነው። በሃጫሉ ሞት ተሳቦ ለሊት ከተኙበት በማንነታቸው ምክንያት በሜንጫ አንገታቸው የታረደ፣ ሬሳቸው የተጎተተ፣ ቤታቸውና ንብረታቸው ዶጋ አመድ የሆነ ኢትዮጵያውያን አስከሬናቸው ሳይነሳ፣ ደማቸው ሳይደርቅ የሰው ሳይሆን የእንሣት መብት በሚከበርበት ዓለም ያሉ ድኩማን ዘረኞች “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” ሲሉ የተመለከተና የሰማ ዓለም ከእንስሣም የወረዱ ደደቦች መሆናቸውን በትዝብት እያስተዋለ ነው።
ሃጫሉ የማንም ዘረኛና ጠባብ ፖለቲከኛ መጠቀምያ ሊሆን አይገባውም። ጸጋዬ አራርሳ፣ ህዝቄል ጋቢሳ፣ ጀዋር ሞሃመድና ሌሎችም የሌላ ብሄር ጽንፈኞች ውጭ እንኳ ሆነው በፍርሃት ሲያረግዱ ወያኔዎች ፊት ሚሊኒየም አዳራሽ ላይ “ቄሮ አላችሁ ወይ? አራት ኪሎ ለእናንተ አይቀርብም ወይ? ፈረሳችሁን ኮልኩሉና ግቡ እንጂ” ብሎ ህወሃቶችን ያስሸና፣ መቀሌ እንዲደበቁ ያስገደደ ጀግና በጽንፈኞችና በሚጸየፋቸው ህወሃቶች ቅንብር የተገደለ ብሄራዊ ጀግና ነው። በእሱ ስም ንጹሃንን መገደል ማለት ትልቅ ውርደት ነው። ከገዳዮቹ ጋር ያበሩ ጽንፈኞች በምንም መልክ የሃጫሉ ተቆርቋሪ አይሆኑም።
የኦሮሞ ጽንፈኞች ምንድን ነው ፍላጎታቸው? በደቂቃዎች ልማቷ የተንኮታኮተ፣ ትምህርት ቤቷ የተቃጠለ፣ ንግድ ተቋሞቿ የነደዱ፣ እንደሶርያ የወደመች ለልጆቿ ስራ የማትፈጥር ኦሮምያን ነው የሚፈልጉት? ጌቶቻቸው ህወሃቶች እንኳን ትግራይ ያለ ተቋም ሊያቃጥሉ ይቅርና መሃል አገር ያለው ዘረፋቸው እንዳይቋረጥ የሞት ሽረት ትግል ሲያደርጉ በጥላቻ የታወሩ የኦሮሞ ጽንፈኞች ኤኮኖሚያቸውን ያወድማሉ። ቤቱን አንድዶ “አሁን ገና በራልኝ” እንዳለው የአእምሮ በሽተኛ በነደዱ የኤኮኖሚ ተቋማትና ዜጎች አመድ ላይ ቆመው ይስቃሉ። ከዚህ የበለጠ ድድብና፣ ከዚህ የወረደ ዝቅጠት የት ይገኛል?
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው እልቂት የዘር እልቂት መሆኑን ማመን የማትፈልጉ መብታችሁ ነው። ሌላውን ለማሳመን የምታደርጉት መፍጨርጨር ግን ከገዳዮች ጎን ይጨምራችኋል።
የሩዋንዳው እልቂት ሲፈጸም አቅም እያለው ምንም ያላደረገው በጊዜው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ የነበረው ኮፊ አናን ጊዜ ካለፈ በኋላ እንዲህ ሲል ተናዟል። “A genocide begins with the killing of one man- not for what he has done, but because of who he is.” (ጥሬ ትርጉሙ የዘር ማጥፋት የሚጀመረው አንድ ሰው በሰራው ሳይሆን በማንነቱ የተገደለ እለት ነው)
ጽንፈኞችንና ዘረኞችን እንተዋቸውና የተማርን ነን የምትሉ ተመጻዳቂ ኢትዮጵያውያን! ኮፊ አናን አንድ ሰው በሰራው ሳይሆን በማንነቱ የተገደለ እለት ዘር ማጥፋት ይጀመራል ብሏችኋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በማንነቱ ስንቱ ሰው ነው የተገደለው? ስንት ቁጥር ላይ ሲደርስ ነው ዘር ማጥፋት ነው የምትሉት?
ኦነግ ሻዕብያ ጋር ተባብሮ አሶሳ ላይ በአዳራሽ አስገብቶ ያረዳቸው አማሮች የተገደሉት በስርቆት ነው?
ህወሃት ጋምቤላ ላይ ከአራት መቶ በላይ ንጹሃን አኝዋኮችን በአንድ ቀን የገደለው በማነነታቸው አይደለም?
አሁንም ኦነግ አርባ ጉጉ ላይ ከነነፍሳቸው ወደገደል የወረወራቸው ህወሃት ከኋላው ሆኖ በፊልም የቀረጻቸው አማሮች ምን አጥፍተው ነው?
ህወሃት ኦጋዴን ላይ በመትረየስና በአውሮፕላን የጨረሳቸው ሶማሌዎች ምን አድርገው ነው?
ደብረ ዘይት ላይ በኢሬቻ በአል በህወሃት ያለቁት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች የተገደሉት ምን አድርገው እንደሆነ የሚነግረን አለ?
ከለውጥ በኋላ አዲስ አበባ ጋሞዎች፣ ጥቅምት ላይ ጁዋር ተከበብህ ሲል ኦሮምያ ያለቁት ወገኖቻችን አሁን ደግሞ ሰኔ 23 ሃጫሉ ከተገደለ በኋላ የታረዱና የተዘረፉ ሰዎች ምን ወንጀል ሰርተው ነው?
በእውነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው በማንነቱ ተለይቶ መገደል ከተጀመረ ቆይቷል። ይህ ሁሉ ዝምታ ሆነ ማስተባበል ገዳዮችን ለመሸፋፈን ከመፈለግ ካልሆነ በቀር የዘር ማጥፋቱ ወንጀል ከትናንት ዛሬ የበለጠ እየሰፋ መጥቶ ኢትዮጵያን ጨርሶ ለማጥፋት መድረሱን አውሮፓና አሜሪካ ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ የሚለው ድምጽ ካላባነነን ሞተናል ማለት ነው። ትንሽ ከቆየንና ምንም እርጃ ካልወሰድን ሁላችንም እንደ ዋልተንጉስ መኮንን ጨለማ ውስጥ እንገባለን።
The post ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ? (አንተነህ መርዕድ) appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.