Quantcast
Channel: , Author at Satenaw: Ethiopian News | Breaking News: Your right to know!
Viewing all articles
Browse latest Browse all 8076

‹‹ሀገሩ ተጎድቶ አዝኖ ስላየችው፣ እምዬ አትጠገብ ካሳን ወለደችው››

$
0
0

‹‹ሀገሩ ተጎድቶ አዝኖ ስላየችው፣

እምዬ አትጠገብ ካሳን ወለደችው››

ባሕር ዳር፡ ጥር 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) የማዕከላዊ መንግሥቱ ደክሟል፣ አንድነት ታሟል፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ ወሰን እየተካለሉ ግዛታቸውን ያሰፋሉ፡፡ ጭሰኛው ለደረሰው መስፍን ሁሉ እየገበረ ስቃዩ በዝቷል፡፡ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሲሻው ያስገብራል፣ ሲሻው እየገረፈ ያስራል፡፡ አቤቱ እውነተኛው ፍርድ ና ፣ መልካም ጊዜ ራቀ፣ የንጉሥ ያለህ የሚለው በርክቷል፡፡

የኢትዮጵያን የውስጥ መዳከም ያዩ ሀገራት ቢችሉ ሊገዟት፣ ባይችሉ ሊዘርፏት መቋመጥ ጀምረዋል፡፡ ሚስጥራዊት፣ ቀደምትና እመቤቷ ኢትዮጵያ አንድነቷን የሚያጠነክር፣ ዘመን የሚያሻግር፣ ማንነቷን የሚያስከበር፣ ታሪኳን የሚዘክር መልካም ንጉሥ አስፈልጓታል፡፡

‹‹በንጉሥ አምላክ፣ በሰንደቁ አምላክ›› እያለ የሚኖረው የሀገሬው ደግ ሕዝብ አምኖት የሚመካበት፣ ተበድሎ አቤት የሚልበት፣ ወዶ የሚገዛለት፣ ፈቅዶ የሚገብርለት፣ ስሙን ጠርቶ የሚመልበት ንጉሥ ናፍቆታል፡፡

የደጎቹንና የጀግኖቹን ኢትዮጵያዊያንን ልመና ሊሰማ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ሊመልስ፣ ኃያል ንጉሥ ሊያነግሥ ሲሻ ከሁለት ደግ ጥንዶች የተገኘ ፍሬ ለኢትዮጵያ ሰጠ፡፡ ፈጣሪ መልካም ፍሬ ሊሰጥ ሲፈልግ ሁለት ደግ ሰዎችን አጣመረ። በምክንያት ተሳሰሩ፡፡ በንፅህና ተገናኙ፡፡

የልደት በዓል አልፏል። በየቤቱ ድግስ ተደግሶ ሲበላና ሲጠጣ ሰንብቷል። የጥምቀት በዓልም ተቃርቧል። ልደትን አሳልፎ ጥምቀትን ለማክበር ሽርጉዱ በዝቷል። የቋራ ባላባት የዓመት ባዕል ሰሞን እርዱና ድግሱ በርክቷል።

በቋራው ባላባት ኃይሉ ወልደጊዮርጊስና በእሜቴ አትጠገብ ቤት ከበዓል መካከል ቤቱን የሚያሞቅ እንቁ ስጦታ መጣ። አብራካቸው ልጅ የናፈቀው እሜቴ አትጠገብ ወረሃ ጥር በገባ በ6ኛው ቀን በ1811 ዓ.ም መልካም ስጦታቸውን ተቀበሉ። ደስታ ሆነ። ቋራ ቻርጌ (ሻርጌ) ማርያም ያ ባለራዕይ የተወለደባት ናት። አስቀድሞ ያወቀ አልነበረም እንጂ ደስታው ለኢትዮጵያም ነበር። ከልቡ የሚያፍቅራት፣ ከልቡ የሚሰራላት፣ የሚያስከብራት፣ የሚያከብራትና የሚያኮራት ጀግና ትሻ ነበርና።

በወረሃ ጥር የተገኜው አይሸነፌ ሕፃን ለእናቱ አንድ ብቻ ነበር። ‹‹አንድ ለእናቱ ሺሕ ለጠላቱ መይሳው ካሳ ሞቱ ኩራቱ›› እንዳለ ከያኙ የእናቴ ልጅ የሚለው ተጨማሪ ወንድም ወይም እህት አልተገኜለትም፡፡

“አንድ ዘር ዘርተን ጎተራ ሙሉ አፈስን” እንዲሉ አንድ ሆኖ ተወልዶ ሺህ ሆኖ ኖረ። ሺህ ሆኖ አስተዳደረ፣ የአንድ የተባረከ መልካም ፍሬ ነውና ስሙ ከፍ አለ። ከፍ ካለበት አልወረደም። የእውነት ሰርቶ የእውነት ነውና ከፍ ያለው።

እሜቴ አትጠገብና ኃይሉ ሀገር የሚከስ፣ ወደፊት የሚገሰግስ፣ ለጠላት የማይመለስ፣ በጦር የማይቀመስ፣ ምሽግ የሚደመስስ፣ ሲጨንቅ ፋጥኖ የሚደርስ መሆኑ አስቀድሞ ታያቸው መሰል ካሳ አሉት። ሀገርም ካሰ። አትጠገብ ካሳን አርግዘው “አንድ ታላቅ ሰው መጥቶ መስቀል ሰጠኝ። መስቀሉንም እቀፊው አለኝ እኔም አቀፍኩት” ብለው ህልም ተናገሩ ይባላል።

ይህን ሕልም ከፍ አድርጎ ያየላቸው አልነበረም። እርሳቸው ግን በልባቸው ይጠብቁት ነበር። ካሳ ተወለደ። ልክ እንደ መስቀሉ ሁሉ አንድ የሚያደርግ፣ ሀገር የሚያስማማ የሚያስታርቅ ሆነ።

ካሳ አንድ ሆኖ ተወልዶ በእናትና በአባት አላደገም። አባቱ በለጋ እድሜው እያለ ነበር የሞቱበት። የነገሥታቱ ዘር እሜቴ አትጠገብ ብልህ ነበሩና ልጃቸው በለጋ እድሜው ትምህርት እንዲማር አደረጉት። አስቀድሞ ለታላቅ ነገር የታጨ ነበርና ከቀለም ጋር ተስማማ፣ የቤተ ክህነቱን ትምህርት በየአድባራቱ እና ገዳማቱ ተዘዋውሮ ጠንቅቆ አጠና። የቤተ መንግሥቱን ሥራ ደግሞ ከአጎቱ ጋር ሆኖ በቋራ ቀሰመ።

ካሳ በቋራ ሲኖር የውጭ ጠላቶች ድንበር ጥሰው ሲገቡ በሚገርም ጀግንነቱና የጦር ስልቱ እየነደፈ ይመልስ ነበር። ጦር ሲወረውር አይስትም። አደን ሲወጣ ያለ ግዳይ አይመለስም፣ ሽምጥ ሲጋልብ አይሸነፍም። ሽንፈት ለካሳ የተገባች አይደለችም። በየሄደበት ሁሉ አሸናፊ ነው።

የሀገሬው ሰውና እረኛው ካሳ ይነግሳል። አንድነት ይመለሳል እያለ ትንቢት ይናገር ጀምር። ካሳም የመሳፍንቱ አገዛዝ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲያንገሸግሸው ያደገ፣ ለሰው ያልገለጠው እንደ እሳት የሚያቃጥለው ሕልም ነበረውና ሕልሙን ለማሳከት በትጋት ይሰራ ጀመር።

ጊዜው ሄደ ጎልማሳው ካሳ የሽፍትነት ስራ ጀመረ። የእርሱ መሸፈት በመንደር ብቻ ተወስኖ ለመቅረት አልነበረም። ጠንክሮ ወጥቶ ኢትዮጵያውያን አንድ ማድረግ እንጂ። ፍፃሜ ዘመነ መሳፍንት ቀረበ። የካሳ ኃይል እያየለ ሄደ። ቋራ ጀግናውን ሰው ይደግፈው ጀመር። ታላቆቹ መሳፍንቶች ስጋት ገባቸው። እቴጌ መነን የዚያ ቋረኛ መጠንከር አልጣማቸውም።የካሳ አካሄድና የዘመኑ ስርዓት ተቃራኒ ስለነበር ካሳ በሚያስደንቅ ጀብዱ ይገሰግስ ጀመር። የካሳ አካሄድ ያላመራቸው መነን ደጅ አዝማች ወንዲራድን እጁን ይዞ እንዲያመጣው ላኩት።

የካሳ ግንባር የሚቻል አልነበረም እና ወንዲይራድ ተሸነፈ። ድንጋጤው የበለጠ አየለ። በወቅቱ በቱርክ ሱልጣን ስር የነበረው የግብፁ ገዢ ሞሐመድ አሊ የግዛት ማስፋፋቱን ተያይዞት ነበር። ሱዳንን በጦርነት አንበርክኮ የማይታለመውን አለመ፣ ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር ለመቀላቀል። ከደጅ አዝማች ክንፈ ጋር ተጋጠመ። ታላቅ ውጊያ ተደርጎ ድሮም ማሸነፍ ማንነት የሆነው የኢትዮጵያ ወገን አሸነፈ። ክንፈ ድል አደረገ።

በዚህ ውጊያም የግብፅ ጦር በሺህ የሚቆጠር ግዳይ ጥሎ ሸሸ ይላሉ የታሪክ ሰዎች። ቀደም ሲል የተሸነፈው የሞሐመድ አሊ በሙሳ ፓሻ የተመራ ሌላ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ዘለቀ። የካሳ ወታደራዊ ዝና በግብፅ ደርሶ ነበርና የጦር መሪው አስቀድሞ ካሳን እንዲይዝ ታዟል። ካሳ ግን አስቀድሞ ተዘጋጅቶ ነበር። መነንም ካሳ እንዲወጋ አዘዙ።

ካሳን ሊወጋ ከሚሄደው ጦረኛ ጋርም ለማዋጋት ትሆን ዘንድ ልዕልቷ ተዋበች አብራ ተላከች። የመነን ጦር ከካሳ ጦር ጋር ሳይገናኝ ከግብፁ ጦር ጋር ተገናኜ። የግብፅ ጦር አይሎ ነበርና የመነንን ጦረኛ ጎዳው። ካሳ በዚህ ወቅት ተበሳጨ፣ ሀገር ተደፍራለችና፣ ህልም ሰነቀ፣ ጦሩን አዘጋጅቶ የግብፅን ጦር ብትንትኑን አወጣው። በግብፅ ጦር እጅ ገብታ የነበረችውን ልዕልቷን አስለቀቀ።

ተዋበች ቁንጅንዋ ወደር አልነበረውም። ራስ አሊ የካሳን ኃይል በለጋው ለመቅጨት አሰበ። በእናቱ በመነን የሚመራ ጦር አዘመተ። ካሳ ድል ቀናው። መነንም ተመራኩ። ካሳ ቋራን እና ደንቢያን ማስተዳደር ጀመረ።

መይሳውን ያልቻሉት እነ ራስ አሊ ልዕልቷን ሰጥተው የካሳን አካሄድ ማስታገስ ፈለጉ። በጋብቻ ተቆራኙት። ያበረዱት መሰላቸው እንጂ ተጨማሪ ኃይል ነበር የሰጡት። በጀግንነቱ ትደነቅ የነበረችው ተዋበች የሀሳቡ ደጋፊ ሆነች።

“ልቦነዋ ነግሯት ታጠቅ እያለችው፣

እምዬ ተዋበች ሰው የነበረውን መላዕክ አረገችው

በታጠቀው ወኔ በማይጠፋው ሕልሙ ኢትዮጵያን ለማቅናት ነበረ ድካሙ››

የካሳ ህልም መሳካት እየገፋ ሄደ። ህልሙ እየቀረበ መጣ። ኃያል ንጉሥ ሲመኝ የነበረው የሀገሬው ደግ ሕዝብ ምኞቱ ሊሰምር ሲል ካሳ ከድል ላይ ድል እየደራረበ ተጓዘ። ዘመነ መሳፍንት አንኮታኩቶ፣ አንዲት ኢትዮጵያን መስርቶ፣ በደረስጌ ማርያም በአቡነ ሰላማ እጅ ንግሥና ተቀብቶ ከልብ አውቃ ሚስቱ ጋር ንጉሠ ነገሥት ሆኖ ዘውድ ጫነ።

መሳፍንቱ የተመኙት ዙፋን፣ የአካባቢ አስተዳደር ባዶ ሆኖ ባለ ራዕዩ ካሳ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብሎ ነገሠበት። በትንቢት ከተነገረውና ከመጣበት ታምራዊ ጀግንነት አንፃር ቴዎድሮስ የሚለውን ስም መረጠ።

በመረጠው ስሙ የተመረጠና የማይጠፋ ሥራ ሰራ። መይሳው የዛሬውን እና የቀጣዩን የኢትዮጵያ ትውልድ በመንፈስ ይገዘዋል ይሉታል። ቴዎድሮስ በዓለማችን ከነገሡት ነገሥታት አገራቸውን ከሚያፈቅሩ ጥቂት ጀግኖችና ታላላቅ መሪዎች መካከል አንደኛው ነውም ይሉታል።

ከዘመን የቀደመ፣ በሩቅ ያለመ፣ ለአገር የደከመ፣ ለአገር የታመመ መሪ ነው። ዘመንን መቅደም ክፉ ነውና የቀደመው ዘመን ሩቅ አሳልሞ ሩቅ ሳይደርስ አስቀረው። መቅደላ ዘግይታ ቢሆን፣ ዘመኑ ከቴዎድሮስ ሩጫ ጋር ቢስተካከል ኖሮ ህልሙ ሁሉ በተሳካ ነበር።

በኢትዮጵያ በቴዎድሮስ አይነት ተነስቶ፣ በቴዎድሮስ አይነት ሰርቶ፣ በቴዎድሮስ አይነት ያለፈ ታላቅ ንጉሥ ቀድሞት አልተፈጠረም ይባላል።

“ለሀገሩ የመጀመሪያውና እርሱ ብቻ የሆነው ሀገሩን አፍቃሪ” ይሉታል። ቴዎድሮስ ፍርሃት ጨርሶ የሌለበት ጀግንነቱና የጦርነት ስልቱ ወዳጆቹም ጠላቶቹም እንዲያደንቁትና እንዲያጨበጭቡለት አድርገውታል ይሉታል። ታላቁ የጥበብ ሰው አቤ ጉበኛ “ለአፄ ቴዎድሮስ ጀግንነት የማንም ብዕር የማንም አፍ ምስክር ከሚሆን እረፍት የሚባል ነገር ሳያውቁ፣ በየአቅጣጫው ተንከራተው አንድ ያደረጉት የኢትዮጵያ አፈር ይመሰክራል” ብለውታል።

መይሳው ዛሬም ጦር ይመራል፣ ዛሬም ስለሀገር ፍቅር ይሰብካል፣ ዛሬም አንድነትን ይመራል፣ የማይጠፋው ህልሙ፣ ያላለቀው ድካሙ ዛሬም ኢትዮጵያውያንን ያነሳሳል።

“እየሞገቱት እየረታቸው

እየገጠሙት እየመታቸው

በታች ሲመጡ በላይ ታያቸው

የበጋ መብረቅ የመላኩ ሰይፍ መሰለባቸው”

ቴዎድሮስ ለአሸናፊነት የተፈጠረ፣ ከዓለት የጠጠረ፣ ከሰው የከበረ፣ ከዘመን አስቀድሞ የበረረ ነው። ቴዎድሮስ አይተባይም፣ አይኮራም፣ አይፈራም። “ያለ ክርስቶስ እኔ ከምንም ነገር አልቆጠርም። ይህን የተዘበራራቀ መንግሥት እንዳጠራውና እንዳሻሽለው ተመርጬ ተሆነ ግን ተርሱ እርዳታ ጋር ይህን እንዳላደርግ ማን ያግደኛል?” ይል እንደነበር በዘመኑ አብረውት የነበሩ መስክረውለታል።

ቴዎድሮስ ዘመነ መሳፍንት የበዘበዛትን ሀገሩን ብቻ ሳይሆን ኢየሩሳሌምን ከግዞት ለማውጣት ያልም የነበረ የጭቁኖች አባት ነበር። ቴዎድሮስ እንደ አካሉ ጥንካሬ የአዕምሮ ጥንካሬም እንደነበረው ይነገርለታል። በዘመኑ ከፍተኛ የነበረውን የሀገሩን ትምህርት በጥልቅ ያወቀ፣ አረብኛ ቋንቋን የሚችል ታላቅ ሰውም ነበር።

ቴዎድሮስ በሀገሩ ጉዳይ እጅግ የበሰለና ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተሻለ እውቀት እንደነበረውም ይነገርለታል። ታላቁ አስተዳዳሪ ቴዎድሮስ እጅግ ሰፊና የአንድነት መንፈስ ያለበት ልብ ነበረው።

ቴዎድሮስ ሌባና ቀማኛ እንዳይኖር፣ ባርያ እየሉ በሰው መነገድ እንዲቀር፣ ወታደርና ሹም ሁሉ በደሞዝ እንዲተዳደር፣ የሰላማዊ ሕዝብ ሰላምና ንብረት በማንም እንዳይደፈር፣ ጉቦ መማለጃ ጨርሶ እንዲጠፋ ያደረገም ነው።

አፄ ቴዎድሮስ የአንድ ታላቅ መሪ ስጦታዎችን ሁሉ የታደለና በጊዜው ይወዳደረዋል የሚባል ኢትዮጵያዊ አለመኖሩም ይነገርለታል። በሀገሩ ለመጣበት እንኳን በጠላቱ በሕይወቱ ላይ ይጨክናል።

ሀገሩ ለእርሱ ከምንም በላይ ናት። የታሪክ ሰዎች ኢትዮጵያ ቴዎድሮስን ባፈራች ጊዜ መንጋ ሳይኖራት እረኛ አበጅታ ነበር ይሉታል። ቆንስል ፕላውዴን “የአእምሮ እና የአካል ጥንካሬያቸው ድካም አይሰማውም። የመንፈሳቸውና የአካላቸው ድፍረት ወሰን የለውም። ሰርተው አይታክታቸውም። ቀንም ይሁን ሌሊት የሚያርፉት በትንሹ ነው። ማመንታት በእርሳቸው ዘንድ አይታወቅም” ብሎታል።

“አትጠገብ ናት የወለደችው

ፍርሃት አያውቅም ምን አበላችው።

የእነ አጅሮች ልጅ ውለታው ብርቱ

በየሄደበት ያስፈራል ፊቱ።

ወንድ ነበረ የእሳት አለሎ

ፍቅሩን ነው እንጂ ጠቡን ማን ችሎ።

ከፈሪ ጋራ የማይስማማው

የልቡ ኩራት እየተሰማው።

ጀግና ነበረ የቀትር እሳት

የአባቱን ሀገር አያስቀምሳት”

ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ “ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለማሰልጠን የነበራቸው ሰፊ ዓላማ በጠላት ፊት ላለመዋረድ ራሳቸውን እስከ ማጥፋት የደረሱበት የቆራጥነት ታሪካቸው ባገር ላይ እንደ አጥቢያ ኮኮብ በሰፊው በኢትዮጵያ ሕዋው ላይ እያበራ ፀዳሉ ያለ ማቋረጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሕያው ሆኖ ይቀጥላል” ብለውለታል።

ጳውሎስ ኞኞ ደግሞ “ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከተለያዩ መኳንንት አገዛዝ አውጥቶ ባንድ መንግሥት ሥር እንድትተዳደር ለማድረግ የጥርጊያውን መንገድ የከፈቱ ዋናው መሐንዲስ ናቸው። ለአጤ ዮሀንስ እና ለአጤ ምኒልክ መጓዣቸውን መንገድ በሕይወታቸው የከፈቱ እሳቸው ናቸው” ብለዋል።

ይህ ስሙ እየገነነ የሚሄደው ታላቁና በላ ራዕዩ ንጉሥ የተወለደው እነሆ በዛሬው ቀን ነበር። እኛም አንድነት ምልክቱ፣ ጀግንነት ማንነቱ፣ ኢትዮጵያዊነት ርስቱ፣ ሺህ ለጠላቱ፣ አንድ ለናቱ የሆነውን የወንዶች ወንድ ልናስበው ወደድን።

የኮራህ ነህና ኮርተንብሃል። በሰራኸው ታሪክ ሁሌም እንደሰታለን። ስምህ ምድርን ሲዞራት ይኖራል። ራይህም ይፈፀማል። እንኳን ተወለደክልን እንኳንም ወለደችህ፣ እንኳንም ኢትዮጵያ አየችህ። ከድካም ማረፍ እንጂ ሞት ላንተ አይስማማም።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post ‹‹ሀገሩ ተጎድቶ አዝኖ ስላየችው፣ እምዬ አትጠገብ ካሳን ወለደችው›› appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 8076

Trending Articles