አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስርዓተ-ፆታ አካታችነት ሀገራዊ ጥናት ላይ ከሲቪል ማህበራት ጋር እየተወያየ ነው።
መጭውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካና ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎ ቦርዱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሴቶች በፓርቲዎች ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎና ፓርቲዎች ስለ ስርዓተ-ፆታ ያላቸውን ሰነዶች የተመለከተ ጥናት አድርጓል።
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ጥናቱ በፓርቲዎቹ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስርዓተ-ፆታ ክፍተት መኖሩን እና ሴቶች በፖለቲካው መድረክ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅ ያለ እንደሆነ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥናቱ 70 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተካተቱ ሲሆን ÷ሴቶችን በአባልነት ለመመልመል እንዲሁም በፓርቲ መዋቅሮች ውስጥ የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎችን በመያዝ ረገድ ሊደረግ የሚችል በፆታ ላይ የተመሰረተ አድልዎን በግልጽ የከለከሉ 6 የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው።
ጥናቱ ካካተታቸው 70 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በ21ዱ ብቻ ነው ሴቶች በፓርቲ መዋቅር ኮሚቴዎች ውስጥ የተካተቱት ተብሏል።
ከእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ሴት መሪ እንዳለው የተገለፀ ሲሆን አንድ ሌላ ፓርቲ ደግሞ ሴት ምክትል መሪ እንዳለው ተጠቅሷል።
ምንም እንኳ 90 በመቶዎቹ ፓርቲዎች አንድ አይነት የስርዓተ-ፆታ እኩልነት ወይም የሴቶች መብቶች ጉዳዮችን በፓርቲያቸው ሰነዶች ውስጥ ቢያካትቱ 15 የሚሆኑት ብቻ በፓርቲያቸው ውስጥ የስርዓተ-ፆታ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚያስችል መዋቅር አላቸው ተብሏል።
ምክትል ሰብሳቢው የሲቪል ማህበራት ይህንን ጥናት መሰረት በማድረግ የሴት ፖለቲከኞችን ቁጥር እና በፓርቲዎች ውስጥ በአመራር ሰጭነት ጭምር የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
The post ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስርዓተ-ፆታ አካታችነት ሀገራዊ ጥናት ላይ ከሲቪል ማህበራት ጋር እየተወያየ ነው appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.