
‹‹ወደላይ፣ ልቤን ሰድደኩት እንዲያይ››
ባሕር ዳር፡ ጥር 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሰማይ ጥበቡ የማይመረመር፣ የብርሃን የሆነ አመስጋኝና ማመስገኛ አለ፣ መላእክት ያመሰግኑበታል፣ አምላካቸውን ይለምኑበታል፣ ለምድር በረከት ያሰጡበታል፣ በመንፈስ የተቃኜ፣ ለመንፈሳዊ ብቻ የሚያገለግል ነው በገና፡፡ መላእክት ሲፈጠሩ የብርሃን በገና ነበራቸው ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ሳጥናኤልም ከክብሩ እስኪወርድ ድረስ በገና ነበረው፡፡ በትቢቱ ከክብሩ ሲወርድ ግን በገናውም ሞገሱም ራቁት፣ ክብሩ ተገፈፈች፣ ሌሎች ቅዱሳን መላእክት ግን እስከነ በገናቸው በክብራቸው ኖሩ፡፡
በገና ጌታ የሚመሰገንበት፣ ምልጃ የሚቀርብበት መንፈሳዊ መሳሪያ ነው፡፡ የበገና ሥርዎ ቃሉ መዝሙር ነው ይላሉ አበው፡፡ ‹‹አቤቱ አስር ክር ባለው በገና አመሰግንሃለሁ›› እንዳለ የበገና ሚስጥራዊ ፍቹ ምግባር ነውም ይላሉ፡፡ ምግባርን ከሃይማኖት ጋር የሚያስተሳስር፣ የሚያጣምር ነው ይሉታል፡፡ ‹‹በገናም አንሱ ከበሮም ስጡ›› እንዳለ ለምስጋና በገና ይደደራል፣ መለከት ይነፋል፣ ከበሮ ይቆረቆራል፣ ፅናፅን ይፀነፀናል፡፡
‹‹በእግዚአብሔር ገነት በኤደን ነበርህ፣ የከበረ ዕንቁስ ሁሉ ስርድዮን፣ ቶጳዝዮን፣ አልማዝ፣ ቢረሌ፣ መረግድ፣ ኢያሳጲድ፣ሰንፔር፣ በሉር፣ የሚያብረቀርቅ እንቁ፣ ወርቅ ልብስህ ነበረ፣ የከበሮህና የእንቢልታህ፣ ሥራ፣ በአንተ ዘንድ ነበረ፣ በተፈጠርክበት ቀን ተዘጋጅቶ ነበር፣ አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፣ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፣ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ፡፡
ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍፁም ነበርህ፣ በንግድህ ብዛት ግፍ በውስጥህ ተመላ፣ ኃጥያትም ሠራህ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ›› እንደተባለው ሳጥናኤል እስከ በደሉ ጊዜ ድረስ የሚያመሰግንበት መሳሪያዎች አብረው ተዘጋጅተውለት ነበር፡፡ እኒህም ማመስጋኛዎች ብርሃናዊ ሰማያዊ ነበሩ እንጂ ምድራዊ አልነበሩም፡፡
በባሕርዳር የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ የበገና ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤትና መምሕር ሊቀ መዘምራን ጌታቸው ብርሃኑ በገና መነሻው ሰማያዊ የሆነ ኢትዮጵያዊያንም ከቀደም ጀምረው ለምስጋና የሚጠቀሙበት መሳሪያ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ በኢየሩሳሌም ዳዊትና ሰለሞን በገና እየደረደሩ አምላካቸውን ያመሰግኑ ነበር፡፡ ዳዊትም ከአባቱ ነው የተማረው፡፡ ሰለሞንም ከዳዊት ተማረው፡፡ በኢትዮጵያ የማክዳ እናት አዝሜኒያ በገና እየደረደረች ፈጣሪዋን ታመሰግን ነበር ይላሉ ሊቃውንት፤ ማክዳና ልጇ ቀደማዊ ሚኒልክ በገና እየደረደሩ ፈጣሪን ያመሰግኑ ነበር ነው የሚሉት ሊቁ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ነገሥታት በገና እየደረደሩ ኃይል ለሆናቸው ለፈጣሪያቸው ምስጋና ያቀርቡ እንደነበርም ሊቀ መዘምራን ነግረውኛል፡፡ ከኃይለ ስላሴ ዘመን መንግስት ወዲህ ግን በገና መደርደር እየቀነሰ መጥቷል፡፡
ዳዊት አስቀድሞ የደረሳቸው መንፈሳዊ መዝሙሮች በገና እየደረደረ ነበር፡፡ ‹‹መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፣ እያንዳንዳቸውም በገናና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ›› አራቱ እንስሳ የተባሉትም ባራ ማራ፣ እግረ ማጣ፣ መሊጦን እና ሱርትዮን ናቸው፡፡ ዳዊት በሰማይም ከጌታ ዙፋን ስር የማይመረመር እፁብ ድንቅ ልብስ ለብሶ በገና እየደረደረ ጌታውን ያመሰግናል፡፡
ታቦተ ፅዮን ከኢየሩሳሌም ስትወጣ በገና ይደረደር እንደነበር ሊቁ ነግረውኛል፡፡ ዛሬም ታቦታት ለጥምቀት ከመንበራቸው ሲወጡ በገና እየተደረደረ ምስጋና ይቀርባል፡፡ ድንግል ማርያም የክብር ሞት ትሞት ዘንድ ልጇ በፈቀደ ጊዜ ‹‹ዕዝራ በማሲንቆ ዳዊት በበገና እያመሰገኗት….›› እንዳሉ በአጠገቧ ሆነው እያመሰገኗት በተመስጦ እያለች ነብሷ ከስጋዋ ተለዬች፣ ጌታም ወደ እርሷ መጥቶ ነበር፡፡ በገና ሚስጥሩ ከፍ ያለ መንፈሳዊ መሳሪያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በገና በሚስጥርና በጥበብ የተሰራ ነው፡፡ ከበግ አንጄት የሚሰሩ አስር አውታር አሉት ፣ ምሳሌያቸውም የአስርቱ ትዕዛዛት ነው፡፡ በቀኝ በኩል ያለው መሰሶ የቅዱስ ሚካኤል፣ የፍቅረ እግዚአብሔር፣ የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ነው፣ በግራ በኩል ያለው ደግሞ የቅዱስ ገብርኤል የፍቅረ ቢስ፣ የሀዲስ ኪዳን ምሳሌ ነው፣ ከላይ ያለው የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው፡፡ ከታች ያለው መወጠሪያ የምድር ምሳሌ ነው፡፡ እኒያ አስርቱ አውታሮች ሰውና እግዚአብሔርን ምድርና ሰማይ የተገናኙበት ማለት ነው፡፡ ከምድር ምሳሌ ከፍ ብሎ የሚገኜው እንዚራዎቹ ያረፉበት አስርቱ ትዕዛዛት ያረፉባት ፅላተ ሙሴ የወረደችበት የሲና ተራራ ምሳሌ ነው፡፡ እንዚራዎቹ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የሚወጣው ድምፅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ሰፊው ቦታ የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡ ቅድስናዋንም ያሳያል፡፡ መቃኜዎቹ ደግሞ ‹‹ለእግዚአብሔር በፍርሃት ሆናችሁ ተገዙ፣ ጥበብንም እወቋት፣ እግዚአብሔር እንዳይቆጣ›› እንዳለ ሲቃኝ ድምፅ አለው፣ ምስጋና ያመጣል ጥበብም ይመጣል ይላሉ አበው፡፡
በገና ከመንፈሳዊ ሕይወት የማይወጣ መነሻው ከሰማይ የሆነ ለዓለማዊ ነገር የማይስማማ እንደሆነም ሊቀ መዘምራን ጌታቸው ነግረውኛል፡፡ ትውልዱ በቀመር ጠፍቷል የሚሉት ሊቀ መዘምሩ ታሪኩን፣ ባሕሉን ሃይማኖቱንና እሴቱን ማወቅ አለበት ነው ያሉት፡፡ ከትምህርት ሁሉ ሀገርኛ ትምህርት መቅደም እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን እናቶች ለቆሎ ተማሪ እንጀራ እየሰጡ፣ ውሻ እየተከላከሉ ታሪክን እንዲማሩ፣ ምስጢር እንዲመረምሩ፣ እንዲያስተምሩ፣ ታሪክ እንዲያቆዩና ራሳቸውን እንዲመስሉ አድርገዋል፡፡
እነሆ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይደርስ ዘንድ በገናው ተነስቷል፣ እየተደረደረም ነው፤ መልካም በዓል፤ ሊቃውንት በበገና እንዲህ እያሉ ያመሰግናሉ፡-
‹‹ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አህዱ አምላክ ብየ ሰላምታ ላድርስ
ኢየሱስ ደግ ባለፀጋ ንጉሥ
ኢየሱስ በአፈ ኩሉ ውዱስ
ኢየሱስ ቅዳሰ ስጋ ወነብስ
ወደላይ ልቤን ሰደድኩት እንዲያይ
ፈጣሪዬ በከንቱ አለቀች እድሜዬ
ሳልገዛ እያሸነፈኝ ስጋዬ
መነሳት ደግሞ አለ ገና ፍርድ መስማት
ደህና ዋሉ፣ ደህና አርፍዱ
የሚያውቅበት አንድም ሰው የለም በፍርዱ
ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
ለዓለም እስከ ዘላለም ድረስ››
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post ‹‹ወደላይ፣ ልቤን ሰድደኩት እንዲያይ›› | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.