Quantcast
Channel: , Author at Satenaw: Ethiopian News | Breaking News: Your right to know!
Viewing all articles
Browse latest Browse all 8076

በአማራ ክልል ሦስት ዞኖች የበረሃ አንበጣ ተከስቷል

$
0
0

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/2012 ዓ.ም (አብመድ) የበረሃ አንበጣ መንጋው ባለፉት ዓመታት ካሳለፏቸው ድርቆች በላይ አሳሳቢ እንደሆነባቸው የስሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡

የበረሃ አንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና እና እንስሳት እርባታ ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ቀጥሏል፡፡ አብመድ ከዚህ በፊት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ባደረገው ቆይታ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ውጤታማው መንገድ እንቁላል ከመጣሉ በፊት በአሰሳ መቆጣጠር መሆኑን አመላክቶ ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የበረሃ አንበጣው በመንጋ መልኩ እንዳይበርር በባህላዊ መንገድና በኪሜካል ርጭት ማጥፋት ነው፡፡ በእነዚህ ዘዴዎች መቆጣጠር ካልተቻለ ግን በሰብል ምርቱ ላይ ጉዳት ማድረሱ እንደማይቀር ሲያስጠነቅቁ እንደነበረ ይታወሳል፡፡

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ ዞኖች እንዲሁም በዋግ ኽምራ ብሔረስብ አስተዳደር በሦስት ዞኖች ላይ የበረሃ አንበጣ መንጋ ተከስቷል፡፡
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስሃላ ሰየምት ወረዳ አንዱ የበረሃ አንበጣ የተከሰተበት ወረዳ ነው፡፡ የወረዳው የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አወጣ ተድላ አንበጣው በመጋቢት ጀምሮ በመንጋ መልክ መከሰት እንደተጀመረ ተናግረዋል፡፡ በስሃላ ሰየምት ወረዳ በሰባት ቀበሌዎች ላይ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ከሌሎች ቦታዎች የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ከዚያው እንቁላል ጥሎ እየተፈለፈለ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በበልግ የበቀለውን ሰብል እያጠፋባቸው፤ በአሸዋማ ቦታዎችም እየተፈለፈለ መሆኑንም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡

የበረሃ አንበጣ መንጋው ባለፉት ዓመታት ካሳለፏቸው ድርቆች በላይ አሳሳቢ መሆኑንም የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የሚቻለውን ለማጥፋት የወረዳው ሕዝብ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያስታወቁት አቶ አወጣ ሕዝቡ መድረስ በማይችላቸው በረሃማ አካባቢዎች ግን በብዛት መፈልፈሉን እና ለማጥፋትም ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው ብሔረሰብ አስተዳደሩም ሆነ ክልሉ የኬሜካል እና ሌሎች ድጋፎች አለማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሰብል ልማት ዳይሬክተር አለባቸው አሊጋዝ ‘‘የበረሃ አንበጣ መንጋው በሦስት ዞኖች ተከስቷል’’ ብለዋል፡፡ አንበጣውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በስጋት ቀጣናዎች የአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች ጋር በቅንጅት እየሠሩ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ በደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ላይ የአፋር ክልል አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች መከሰቱንም አስታውቀዋል፡፡ የተከሰተባቸው ወረዳዎች የእንስሳት ግጦሽ እና የሰዎች እንቅስቃሴ የሚዘወተርባቸው በመሆኑ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ማድረግ አለመቻሉንም አቶ አለባቸው ገልጸዋል፡፡ በወረባቦ አካባቢ የተፈለፈለውን አንበጣ ግን በኬሜካል እና በባህላዊ መንገድ እየተከላከሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስሃላ ሰየምት ወረዳ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ መኖሩን መስማታቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የስሃላ ሰየምት ወረዳ የግብርና ኃላፊ አንበጣው በአሸዋማና በረሃማ ቦታዎች እንቁላል እየጣለ፣ እየተፈለፈለ ከአቅማችን በላይ ሁኗል ላሉት ሀሳብ ‘‘ከአቅማቸው በላይ አይመስለኝም’’ ብለዋል፡፡

የኬሜካል እና የመከላከያ ግብዓት ለጠየቁትም አቶ አለባቸው ሲመልሱ ‘‘ከኮምቦልቻ የዕፅዋት ክሊኒክ እንዲወስዱ’’ ትዕዛዝ መተላለፉን ገልጸዋል፡፡ በሰብል ልማቱ ላይ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል መተንበዩን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ጉዳቱን ለመቀነስ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የበረሃ አንበጣው ሳይከሰት ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸው በተደጋጋሚ ቢገለጽም እንደምሁራኑ ምክረ ሐሳብ እንቁላሉ ሳይፈለፈል ለማጥፋት የተደረገው ጥረት ሳሃላ ሰየምት አካባቢ የተሳካ አይመስልም፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በድጋሚ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ በጠቅላላው 1 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረትና ረሃብ ሊዳረግ እንደሚችል የዓለም የእርሻ ድርጅት በቅርቡ አስተጠንቅቋል፡፡ በአንበጣ መንጋው የአምስት ክልል ሰዎች ተጋላጭ ይሆናሉ ያለው ድርጅቱ በአማራ ክልል 72 ሺህ ሰዎች ለከፋ ችግር ሊጋለጡ እንደሚችል ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ የእንስሳት ግጦሽ ላይም የበረሃ አንበጣው የከፋ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ቅድመ መከላከል ሥራዎች በትኩረት ሊሠራባቸው ይገባል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ፎቶ፡- ስሃላ ሰየምት ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት

The post በአማራ ክልል ሦስት ዞኖች የበረሃ አንበጣ ተከስቷል appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 8076

Trending Articles