የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን በማራዘሙ ወደ አመፅ የሚያመራ ሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሊፈጥር እንደሚችል፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሥጋት አለን አሉ፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ሰሞኑን ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ውሳኔው ሕገ መንግሥቱን ከመጣሱም በላይ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ከመጀመሪያውም ጀምሮ ሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ዘመን ማራዘም የማይፈቅድ መሆኑን ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ በመሆኑም አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረባችን የሚታወስ ነው፡፡ መንግሥት ያቀረበውን አማራጭ በመቃወም ሌላ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ብናቀርብም፣ መንግሥት በተናጠል ውሳኔው ፀንቶ የተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ካውንስል መርቶታል፤›› ብለው፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የመንግሥትን አቋም ከሚደግፉ ባለሙያዎች ጋር ብቻ የይስሙላ ውይይት (amicus curiae) ላይ የተለየ ምልከታ ያላቸው የመደመጥ ዕድል ተነፍገዋል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የጥቅም ግጭትን የማስቀረት መርህ ተጥሶም ውሳኔው የመንግሥትን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ መሆኑ አይገርምም ሲሉ በጋራ መግለጫቸው አክለዋል፡፡
ከመሠረታዊ የውክልና ዴሞክራሲ መገለጫዎች አንደኛው በመደበኛነት በተወሰነ ጊዜ ምርጫ ማካሄድ፣ የተመረጡትም የሕዝብ ተወካዮች የሥራ ዘመናቸው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መሆኑንና የሥራ ዘመናቸውም ሲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን ይለቃሉ ሲሉ፣ ኦነግና ኦፌኮ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ለነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕቅድ ተይዞለት እንደነበር የሚታወስ እንደሆነ፣ ሆኖም ምርጫ ቦርድ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል በእንቅስቃሴና በመሰብሰብ ላይ ገደብ በመጣሉ ምርጫ ለማካሄድ እንደማይችል መግለጹን፣ በወቅቱ ምርጫን ለማራዘም ምንም ዓይነት የሕገ መንግሥት መሠረት ሳይኖር አጠቃላይ ምርጫን ማንሳፈፍ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ የሚያስከትልና ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ አዲስ የተመረጠ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይኖር ማንኛውም መንግሥታዊ ውሳኔና ድርጊት በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጠውን የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን የሚጥስ ይሆናል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) እና 58(3)፣ እንዲሁም የምርጫ ሕጉ አንቀጽ 7 ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መደረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የምርጫ ጊዜን ለማራዘም በር የሚከፍት ነገር አያሳይም፤›› በማለት በጋራ መግለጫቸው ሙግት አቅርበዋል፡፡
በ1987 ዓ.ም. የፀደቀው ሕገ መንግሥት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና በየጊዜው የሚደረግ መደበኛ ምርጫን በአገሪቱ ዕውን ያደረገ መሆኑን፣ የሕዝቦችን በመንግሥት አስተዳደር የፖለቲካ ተሳትፎ በሚያረጋግጥ መርህ የተቃኘ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ብዝኃነትን እንደ ወሳኝ መርህ የተቀበለ መሆኑን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብትና ተግባራትም ከሕገ መንግሥቱ የተቀዱ ሆነው በአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ ሕግ ውስጥ መካተታቸውን ኦነግና ኦፌኮ በጋራ መግለጫው ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ምኅዳር ውስጥ ተመዝገበው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ከላይ በተጠቀሱት ሕጎችና መርሆዎች መመራት አለባቸው ብለው፣ ‹‹ስለሆነም የአካባቢያዊና የፌዴራል ምርጫን በተናጠል በአንድ ፓርቲ ብቻ የማራዘም ሥልጣንን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በዚህ መንግሥት ለሕዝብ የተገባው ቃል በመታጠፉ በቋፍ ላይ ያለውን የሕዝብን ቅራኔ የሚያባብስ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ወደ አመፅ ሊያመራ የሚችል ሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ሥጋታችንን መግለጽ እንወዳለን፡፡ ይህም ወደ አደባባይ የሚመልሰን ብቻ ሳይሆን ከዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የኅብረተሰብ ጤና ተግዳሮቶች ጋር እየተጋፈጠ ላለው መንግሥት ችግሩን ለመቆጣጠር አዳጋች ይሆናል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ የእነሱንና የሌሎችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመፍትሔ ሐሳብ፣ እንዲሁም የዜጎች ጥሪ ሙሉ በሙሉ ቸል መባሉ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሚከሰት ሕገ መንግሥታዊ ቀውስን ለማስቀረት፣ ሁሉን አካታች የፖለቲካ ውይይት አለማድረጉ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
‹‹የገዥው ፓርቲ የራሱን መንግሥት የሥራ ዘመን በተናጠል የማራዘም ውሳኔ ግልጽ የሆነ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ከመሆኑም በላይ፣ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀምም ነው ብለን እናምናለን፡፡ በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ ከተረጋገጠው የዴሞክራሲና የመድበለ ፓርቲ የመንግሥት አስተዳደር መርህ ጋር የሚፃረር ከመሆኑም በላይ፣ በመንግሥት ኃላፊነት የተወሰነ የሥራ ዘመን የሚለውን የሕገ መንግሥት መርሆን የሚሸረሽር ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ገዥው ፓርቲ በተናጠልና ኢሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ የመንግሥት የሥራ ዘመንን ለማራዘም መወሰኑን አጥብቀው እንደሚቃወሙ፣ አሁንም ገዥው ፓርቲ መድረክ አመቻችቶ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጥልቀት ተወያይቶ መፍትሔ በማመንጨት ፖለቲካዊ መግባባት ላይ ይደረስ ዘንድ ጥሪያቸውን ማቅረባቸውን ኦነግና ኦፌኮ በጋራ መግለጫቸው አስረድተዋል።
በጋዜጣዉ ሪፓርተር
The post ኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) እና የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.