
የዓባይ ወንዝ መነሻን በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እየሠራ መሆኑን የሰከላ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሦስተኛውን የግዮን በዓል በድምቀት በማክበር ሥፍራውን ለጎብኚዎች ለማስተዋወቅ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የታላቁ ዓባይ ወንዝ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ ከግሺ ተራራ ሥር እንደሚፈልቅ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ቦታውን ለዓለም ለማስተዋወቅ እንዲሁም ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን በዓለም የቅርስነት (በዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ጥር 13/2013 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የግዮን በዓልን ለ3ኛ ጊዜ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሰከላ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ አገሬ አናጋው ተናግረዋል።
በሰከላ ወረዳ የታላቁ ዓባይ ወንዝ መነሻ ምንጭ፣ ግሺ ተራራ፣ የጉደራ ሐይቅ፣ አርሲታ ዋሻ፣ የፋሲል ግንብ (የአባ ግፍ ጅምር ግንብ)፣ ትክል ድንጋዮች፣ የአላዛር ዋሻ፣ ድንጋይ ቀዳዳ እና ሌሎች የመስህብ ሀብቶች መኖራቸው ተገልጿል፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ያለ በመሆኑ ቅርሶችን ለማስተዋወቅ እንቅፋት እንደሆነ ኀላፊዋ ገልጸዋል፡፡
የግዮን (የአቡነ ዘር አብሩክ በዓል) መከበር ከጀመረ ወዲህ ወረዳው የአስፓልት መንገድ እድል ማግኘቱን እና የመብራት ሁኔታውን ለማሻሻል መንግሥት እየሠራ በመሆኑ ለቀጣይ ምቹ ሁኔታን እንዲሚፈጥርላቸውም ኀላፊዋ ጠቁመዋል።
የግዮን በዓል በሚከበርበት ወቅት የኮሮናቫይረስ ስርጭት እንዳይተስፋፋ ኀብረተሰቡ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ወይዘሮ አገሬ አስታውቀዋል፡፡
ከሌላ ቦታ የሚመጡ እንግዶች የሚያርፉባቸው ሆቴሎችም የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለእንግዶች እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነውም ብለዋል። የግዮን ( የአቡነ ዘር አቡሩክ በዓል) ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
የወጣቶች እና የልጃገረዶች ባህላዊ ጨዋታዎች፣ የገና ጨዋታ፣ የፈረስ ሸርጥ (ግልቢያ) የበዓሉ ድምቀቶች መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ለበዓሉ የበለጠ ድምቀት ለመስጠት በዋዜማው ስፖርታዊ ትርኢቶች እና የሩጫ ውድድርም ይካሄዳል ተብሏል። በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ከፀጥታ አካላት፣ ከወጣቶች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ – ከምዕራብ ጎጃም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post የዓባይ ወንዝ መነሻን በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እየሠራ መሆኑን የሰከላ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.