
ዓለም ባንክ ኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የጀመረቻቸውን ሥራዎች መደገፉን እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር በዶክተር ኦስማን ዲዮን ከተመራው የአለም ባንክ የሉዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ.ር) ዓለም ባንክ በተለያዩ ዘርፎች በኢትዮጵያ በተለይም በዲጂታል ፋውንዴሽን ሥራ እና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚከናወኑ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ያሳየውን ፍላጎትና ድጋፍ አድንቀዋል።
በዉይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን ሙሀመድ (ዶ.ር) በዲጂታል 2025 መርኃ ግብር ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የዲጂታል አሰራርን ለመዘርጋት የሠራችውን ተግባር ለሉዑካን ቡድኑ አብራርተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በመርኃ ግብሩ ዙሪያ ወደ ትግበራ ለመግባት ከልዩ ልዩ አካላት ጋር ድጋፍና ትብብር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቀናጅቶ ለመሥራት የልየታ ሥራ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተወካዩ አለም ባንክ በኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው በተለያዩ ሀገራት ካገኟቸው ተሞክሮዎች አንጻር የዲጂታል አጀንዳን ትግብራ ለማረጋገጥ የተሻለ ጅምር እንዳለ ተናግረዋል።
በተለይም ቬትናም የዓለም ባንክ ፕሮግራም በሚመሩበት ወቅት ካላቸው ልምድ አንጻር በኢትዮጵያ ያለው ጅምር ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።
ዓለም ባንክ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በከተማና ትራንስፖርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ለማዘመን በኢትዮጵያ የሚደረገውን ጥረት ከመንግሥት ጎን በመሆን እንደሚደግፍ መናገራቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጀመራቸውን የተለያዩ መርኃ ግብሮችን ውጤታማ ለማድረግ የዓለም ባንክ የቴክኖሎጂ አማካሪዎች ቡድን ለመመደብ ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post ዓለም ባንክ ኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የጀመረቻቸውን ሥራዎች መደገፉን እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡ appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.