
በሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ሲና ቆሎ ብራንድ (ልዩ መታወቂያ) ተሰጥቶት አውሮፓ ገበያ ደርሷል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሲናን አልፈው የሚሄዱ የህዝብ መጓጓዣ መኪኖች ደብረሲና ሲደርሱ ተጓዦች በመስኮት በኩል ዘወር ካሉ ሴቶች በጣእም ያዘጋጁትን ቆሎ በስፌትና በመስፈሪቸው ይዘው ቆሎ ቆሎ እያሉ መንገደኛው እዲገዛቸው ይጋብዛሉ፡፡ ቆሎ የሚወድ ማንኛውም መንገደኛ ደብረሲና ደርሶ ቆሎ ገዝቶ ሳይበላም አያልፍም ምክንቱም የደብረሲና ቆሎ በጣእሙ ይታወቃልና፡፡

የደብረሲና ቆሎ ለአካባቢው እና ለመንገደኞች ብቻ ሆኖ አልቀረም አውሮፓ ገብያ ላይም ደርሷል፡፡ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ግርማ በደብረሲና ከተማ የ03 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ቆሎ በማዘጋጀትና ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ያገኛሉ፡፡ የሚያዘጋጁት ቆሎ ጥሩ ጣዕም እንዲኖረው በደንበኞቻቸው ዘንድ ተመራጭ እንወዲሆን እና ሳይለዝ ተፈጥሯዊ ጣዕሙን ይዞ እንዲቆይ በጥንቃቄ እደሚዘጋጁት ነው የነገሩን፡፡
ወይዘሮ ጥሩወርቅን ለአብነት አነሳን እንጂ ቆሎ በደብረሲና ለበርካታ ሴቶች ዋንኛ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ በርካቶች ቆሎ በማዘጋጀት ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ደንበኞቻቸው ያስረክባሉ።
በተለይ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ሴቶች በማኅበር ተደራጅተው በጥራትና በብዛት ወደ ገበያ ማስገባት ጀምረዋል። በዚህ ጊዜም ከ400 በላይ ሴቶች በማኅበሩ ተካትተው ማሽን በማስገባት እየሠሩ መሆኑን ነው ከጣርማ በር ወረዳ ኅብረት ሥራ መኅበር ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ የሚያመላክተው።
ይህ ተግባራቸው የደብረሲና ቆሎ ብራንድ (የልዩ እውቅና ባለቤት) እንዲሆን አድርጎታል። በማህበር የተደራጁ ቆሎ ነጋዴወች እደሚሉት የደብረሲና ቆሎ ብራንድ(ልዩ መታወቂያ) ማግኘቱ አስደስቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የማምረቻና መሸጫ ቦታ እጥረት ችግር ሆኖባቸዋል፡፡
የጣርማ በር ወረዳ ኅብረት ሥራ መኅበር ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት የማኅበራት ማስፋፊያ የሥራ ሂደት አስተባባሪ በሪሁን ደሳለኝ በሰጡት ምላሽ በማህበር የተደራጁ የቆሎ ነጋዴወችን ችግር ለመፍታት ለቆሎ ሽያጩ ተጨማሪ የገበያ ማፈላለግ እና ለሥራ እድል ምንጭ እዲሆን ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

በዚህም የደብረሲና ቆሎ በብዛት ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በማከፋፈል ወደ ደሴ፣ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወደ ደቡብ ክልል እና ሌሎችም አካባቢዎች ለገብያ እቀረበ ነው፡፡ በየለያዩ አካባቢዎች በሚዘጋጁ ባዛሮችም እየተዋወቀ ይገኛል፡፡
በዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የሰብል ግብይት ቡድን መሪ ኢሳው ዘለቀ እንደተናገሩት በሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና ምርቶችን የማስተዋወቅና ብራንድ (ልዩ መታወቂያ) እዲያገኑ ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በተሠራው ሥራ የጅሩ ሰንጋ፣ የደብረሲና ቆሎ፣ የምንጃር ጤፍ፣ የአረርቲ ሽምብራ፣ የአንጎለላ እና የመንዝ በግ ዝርያዎች ዝርዝር ጥናት ተሠርቶላቸውና የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልተው በኢትዮጵያ አዕሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የብራንድነት እውቅና አግኝተዋል። ተጨማሪ ምርቶች የዞኑ መለያ ተብለው እውቅና እንዲሰጣቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
በዞኑ በሰባት ወረዳዎች በስፋት የሚገኘው ጦስኝና ምሥር እውቅና እንዲሰጣቸው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ጥናት ተሠርቷል። የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጥናቱን ያጠናቀቀው ሲሆን በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን አቶ ኢሳው ተናግረዋል።
በዞኑ ካሉ አካባቢዎች 50 በመቶ የሚሆኑት በስፋት የሚያመርቱትና ለውጪ ገበያ የሚቀርበው የማሾ ምርትም እውቅና ሲያገኝ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል። ለምርቶች ብራንድ (ልዩ መታወቂያ) ከመስጠት ባለፈ በስፋትና በጥራት ወደ ገበያ እንዲገቡ፣ በኢኮኖሚው ላይ ሚናቸው እንዲጎላና የሥራ ዕድል እዲገኝባቸው ዘርፎቹን የማጠናከር፣ የመደገፍና የመከታተል ሥራው ትኩረት ይሠጠዋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ – ከደብረብርሃን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post በሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ሲና ቆሎ ብራንድ (ልዩ መታወቂያ) ተሰጥቶት አውሮፓ ገበያ ደርሷል፡፡ appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.