
ኢትዮጵያን በቀጣይ 10 ዓመታት የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ተመራቂ ተማሪዎች በሀገሪቱ ልማት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያን በቀጣይ 10 ዓመታት የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የሚያስችል የብልፅግና የልማት ስትራቴጂዎች ተቀርፀው እየተተገበሩ ነው ብለዋል፡፡
ለእቅዱ መሳካት በእውቀት የበለፀገ የሰው ኀይል ያስፈልጋል፤ በመሆኑም ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ዛሬ ተማሪዎችን ያስመረቀው የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ እዲበቃ መንግሥት ከሚያደርገው የግብዓት ማሟላት በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኀላፊዎችና መምህራን በቁርጠኝነት የሠራችሁት ሥራ የሚደነቅ ነው” ብለዋል የጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር፡፡
የጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተመራቂ ተማሪዎችም ለታቀደው የብልፅግና ጉዞ የተማሩትን እውቀት ተጠቅመው ሥራ ፈጣሪ በመሆን በልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ለተመራቂዎች መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ተመራቂ ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ በምትጀምሩት አዲስ የህይወት መንገድ በርካታ ችግሮች ሊገጥሟችሁ ይችላሉ፤ በተማራችሁት እውቀት ፈተናዎችን በጥንካሬ በማለፍ ስኬታማ ህይወት ለመምራት መጣር አለባችሁ ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ለአስመራቂ ወላጆች ባስተላለፉት መልዕክትም መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በመገኘታችሁ የአማራ ሕዝብ እንግዳ አክባሪና አቃፊ መሆኑን ትገነዘባላችሁ ነው ያሉት፡፡
በአማራ ሕዝብ ላይ የተሠራው የሀሰት ትርክት የተሳሳተ መሆኑን ለመመስከር ወሎ እንደ አንድ ማሳይ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሸምስያ በሪሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post ኢትዮጵያን በቀጣይ 10 ዓመታት የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ተመራቂ ተማሪዎች በሀገሪቱ ልማት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ፡፡ appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.