
የፖለቲካ ሽግግሩ በታሰበው ልክ ለውጥ እያመጣ አለመሆኑን የፖለቲካ ምሁራን ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በህዝቦች መካከል አብሮነትን መገንባት ላይ ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ በባሕርዳር እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና የሃይማኖት አባቶች የፖለቲካ ሽግግር ሂደቱና ያገጠሙትን ተግዳሮቶች መነሻ በማድረግ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እየመከሩ ነው::
ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ በ2010 ዓ.ም የተጀመረው የፖለቲካ ሽግግር የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ ውጭ ሀገር የነበሩ የፖለቲካ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ በማድረግና የኢትዮ ኤርትራን ችግር በመፍታት ለውጦች ታይተው ነበር።
ይሁን እንጂ የሽግግር ሂደቱ ህዝቡ በጠበቀው ልክ መጓዝ አለመቻሉን በጽሑፋቸው አሳይተዋል:: የዜጎች ሞትና መፈናቀል እየጨመረ መምጣቱንም በአንክሮ በጽሑፉ አመላክተዋል::
የፖለቲካ ሽግግሩ በታሰበው ልክ ለውጥ እያመጣ አለመሆኑንም አመላክተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተስፋሁን አለምነህ ዜጎች ሀገር ሰላም ብለው በተኙበት በዘራቸው ምክንያት በሚገደሉበት ሀገር ውስጥ ሆነን ለውጥ አለ ማለት አይቻልም ብለዋል።
አቶ ተስፋሁን በዜጎች ሞትና ግድያ ስልጣን መያዝም ይሁን ስልጣንን ማራዘም እንደማይቻል ተናግረዋል። ተፎካካሪ የፖለተካ ፓርቲዎችም የዜጎችን ደኅንነት ከሚጎዱ ተግባራትና ሃሳቦችን ከማራመድ ሊቆጠቡ እንደሚገባ ገልጸዋል::
ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አርቲስት ደሳለኝ ኀይሉ በሀገሪቱ እየተፈፀመ ላለው ጥፋት የፖለቲከኞች ችግር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል::
አርቲስት ደሳለኝ ፖለቲከኞች የራሳቸውን የተደላደለ ኑሮ ለመኖር ኢትዮጵያውንን ለከፋ ችግር ዳርገውናልም ይላሉ::
ፓለቲከኞች ዜጎች በሀገራቸው እንደ ባእድ እየተቆጠሩ ውጣልኝ የሚባሉበት፤ በግፍ የሚገደሉበት ጊዜ ላይ አደረሱን ሲሉም የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል ::
አርቲስት ደሳለኝ ሀገሪቱን ከገባችበት ከባድ ችግር ውስጥ ለማስወጣት ከብሔር ፖለቲካ ወጥቶ የዜግነት ፖለቲካን መተግበር፤ ጠንካራ የሲቪክ ማህበረሰብ መፍጠርና ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ በየተኛውም አካባቢ በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጥር ያስፈልጋል ብለዋል::
ዘጋቢ:– ዘላለም አስፋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post የፖለቲካ ሽግግሩ በታሰበው ልክ ለውጥ እያመጣ አለመሆኑን የፖለቲካ ምሁራን ተናገሩ። appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.