
በምንጃር ሸንኮራ የጥምቀት በዓል በድምቀት ይከበራል፤የወንዙ ሥሪት አምሳለ ዮርዳኖስ መሆኑ ደግሞ ለበዓሉ ልዩ ድባብ ያጎናጽፈዋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ሥፍራው የሚያቀኑ እንግዶችን በአግባቡ ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አስታወቀ። በአማራ ክልል የጥምቀት በዓል ደምቆ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል ምንጃር ሸንኮራ አንዱ ነው።
በዓለ ጥምቀቱ በወረዳው በሚገኝ የሸንኮራ ወንዝ 44 ታቦታት አንድ ላይ በተሰባሰቡበት ይከበራል። 44ቱ ታቦታት እስከ 18 ኪሎ ሜትር ድረስ ተጉዘው ነው በጥምቀተ ባህሩ የታቦታት ማደሪያ የሚሰባሰቡት።

የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋልተንጉስ ዘርጋው “በምንጃር ሸንኮራ የጥምቀት በዓል በድምቀት ይከበራል፤የወንዙ ሥሪት አምሳለ ዮርዳኖስ መሆኑ ለበዓሉ ልዩ ድባብ ያጎናጽፈዋል” ብለዋል፡፡
ወንዙ ከላይ አንድ ሆኖ ከፈሰሰ በኋላ በዓለ ጥምቀቱ በሚከበርበት አካባቢ ለሁለት ተከፍሎ ከታች ሲደርስ ደግሞ ተመልሶ ይቀላቀላል። ይሕም በቦታው የሚከበረውን የጥምቀት በዓል የተለየ ሃይማኖታዊ ድባብ ያጎናጽፈዋል፣ ምዕመኑ የተለየ ስሜት እንዲፈጠርበትም ያደርጋል ብለዋል አቶ ዋልተንጉስ።

ይሁን እንጂ የማስተዋወቅ ሥራ እምብዛም ስላልተሠራበት ቀደም ሲል በዓሉን ለማክበር ከሌላ አካባቢ ወደ ሥፍራው የሚያቀኑ የእንግዶች ቁጥር ዝቅተኛ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተለይ ከአዲስ አበባ እና ከዙሪያው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንግዶች በዓሉን ለማክበር ወደ ምንጃር ሸንኮራ እንደሚያቀኑ ነው ኀላፊው ያስታወቁት።
የፊታችን ጥር 10 እና 11/2013 ዓ.ም የከተራን እና የጥምቀት በዓላትን በድምቀት ለማክበር ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአረርቲ ከተማ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለምንም ዋጋ ጭማሪ በተለመደው እንግዳ አክባሪነት ባህላቸው እንግዶችን እንዲያስተናግዱ ግንዛቤ መፈጠሩንም ነግረውናል።
በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት መኖሩንም ነው አቶ ዋልተንጉስ የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ – ከሰሜን ሸዋ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post በምንጃር ሸንኮራ የጥምቀት በዓል በድምቀት ይከበራል፤የወንዙ ሥሪት አምሳለ ዮርዳኖስ መሆኑ ደግሞ ለበዓሉ ልዩ ድባብ ያጎናጽፈዋል፡፡ appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.