Quantcast
Channel: , Author at Satenaw: Ethiopian News | Breaking News: Your right to know!
Viewing all articles
Browse latest Browse all 8076

‹‹ እንግዳ ሲመጣ አገው ምድር ሲደርስ ፣ አዲናስ ይላሉ ቀልብን በሚሰርቁ በሚያማምር ፈረስ።››

$
0
0

‹‹ እንግዳ ሲመጣ አገው ምድር ሲደርስ

አዲናስ ይላሉ ቀልብን በሚሰርቁ በሚያማምር ፈረስ››

ባሕር ዳር፡ ጥር 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያዊነት ማፍቀር፣ ኢትዮጵያዊነት ማክብር፣ ኢትዮጵያዊነት ስለ እውነት መኖር፣ ኢትዮጵያዊነት ለአሸናፊነት መፈጠር፣ ኢትዮጵያዊነት በፀጋ መክበር፣ ኢትዮጵያዊነት ለሰውና ለነገ መኖር ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ሰውነት፣ ኢትዮጵያዊነት እውነት፣ ኢትዮጵያዊነት እኛነት፣ ኢትዮጵያዊነት አርቆ አሳቢነት፣ ኢትዮጵያዊነት ቀደምትነት፣ ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት፣ ኢትዮጵያዊነት አዛኝነት፣ ኢትዮጵያዊነት ደግነት ነው፡፡

የኢትዮጵያን የመከራ ቀንበር የሚሸከም፣ ጨለማን የሚያሻግር ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያልተሠራ ክፋት ባይኖርም በኢትዮጵያዊነት ያልተሸነፈ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት አመፀኛን ያሸንፋል፣ መከራን ያሳልፋል፣ የተደፋን አንገት ያቃናል፣ በኢትዮጵያ የተሠሩ አኩሪ ታሪኮች ሁሉ መነሻቸው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡

ነጭ ጤፍ የሚበላ፣ ነጭ ፈረስ የሚጭን፣ ከከዘራ ጋር ነጭ ጭራ የሚነሰንስ፣ ነጭ ልብስ የሚለብስ ኩሩና አመስጋኝ ሕዝብ ነው፡፡ ሰው በእንግድነት ሲሄድ ‹‹አዲናስ›› ወይም እንኳን ደህና መጣችሁ እያሉ ይቀበላሉ፡፡ ብቻን መብላት፣ ሰውን መጥላት፣ ከአንዱ አንዱ ማዳላት አይታወቅም፤ ይህ መገለጫ ነው፡፡ በአገው ምድር እንግዳ ተቀባይነት፣ ሰው ወዳድነት፣ የማይደበዝዝ ኢትዮጵያዊነት ሕይወት ነው፡፡ በሰፊው እያረሱ፣ ሳያጎድሉ በበረከት እያፈሱ፣ ሳይሰስቱ እያጎረሱ፣ አሞናሙነው እያለበሱ፣ ሀገር ሲነካ ወገን ሲደፈርም አነጣጥረው እየተኮሱ በበረከት ምድር በበረከት የሚኖሩ ናቸው፡፡

በዚችው ምድር ከደጎች የወጡ ደግ ሰው አግኝተናል፡፡ ብዙነህ ቦጋለ ይባላሉ ፡፡ ነዋሪነታቸው እንጅባራ ከተማ ነው፡፡ የተሰማሩበት ሙያ ንግድ ነው፡፡ እኒህ ሰው ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነት ይቅደም ይላሉ ይሏቸዋል፡፡ እሳቸውም መቅደም ያለበት ኢትዮጵያዊነትና ሰውነት ነው ብለውኛል፡፡ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራ ሲጀምር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን እና ኢትዮጵያዊነትን ይመለከታሉ፡፡ አስቀድመው ኢትዮጵያዊነትን የሚወዱት ብዙነህ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሲያይዋቸው የልባቸውን አገኙት፡፡ አንድ አጋጣሚም የበርካታ ኢትዮጵያዊያን አባት እንዲሆኑ አደረጋቸው፡፡

‹‹ በአንድ ወቅት በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ አመሻሽ ላይ ለሽርሽር ወጥቸ ነበር፤ ዕለቱም ዓመታዊ በዓል ነበር፣ ልጆች ሲጨናነቁ አየኋቸው፡፡ ምን ሆናችሁ ነው? እንጅባራ እኮ ጥሩ ሀገር ነው፤ ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ ነው፣ እንዳትፈሩ ትምህርታችሁን ጠንክራችሁ ተማሩ አልኳቸው፤ ተግባባን፤ ቤቴ እንድትመጡ አልኳቸው፣ ወደቤቴ መጡ፣ አስተናገድኳቸው፣ ከዚያ በኋላ ልጅ ሆኑ፣ ሊጠይቁኝ ይመጣሉ፤ በቃ አብረን ከረምን›› ብለዋል፡፡

ልጆቹ ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸውን ነግረውኛል፣ በአንደኛ ዓመት የጀመረው ወዳጅነት እስከ ምርቃት ጊዜ ዘልቋል፡፡ ጊዜው ደርሶ ልጆቹ የምርቃት ዝግጅታቸውን በልብ ኢትዮጵያዊ አባታቸው ሊያከብሩ ሽርጉድ ላይ ናቸው፡፡

‹‹ ግንኙነታችን የአባትና ልጅ ነው፣ ጓዳ የለም፣ መኝታ ቤት የለም፣ ቤቴ ቤታቸው ነው›› ይላሉ አቶ ብዙነህ፡፡

ስለ ኢትዮጵያዊነት ‹‹ የእኔ ራዕይና ዓላማ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ነው፡፡ እኛ ብሔር ብሔረሰቦች ተባብረን እና ተሳስበን በጋራ ካልኖርን አስቸጋሪ ነው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአካባቢው ባለ ዩኒቨርሲቲ የሚመጡ ተማሪዎችን አራት አምስት ልጅ ይዞ በዓል አብሮ ቢውል፣ ሁሉም ቤተሰብ ሆኖ መጥፎውን ዘር በአጭሩ መቅጨት እንችላለን›› ነው ያሉት፡፡

መልካምነት እና አቃፊነት ካለ ግጭቶች አይኖሩም ነው ያሉት፡፡ መለመድ ያለበትም ይሄ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ማመን አለበት፣ የእከሌ ዘር ነኝ ማለት አይጠቅመንም፣ ድሮም ተባብረው፣ ተቀራርበው፣ ተጠራርተው ሲያበሉ ነው አባቶቻችን የምናውቀው፣ ሲያባርሩ ሲጋደሉ አላየንም፣ ኢትዮጵያን ተባብረን መለወጥ አለብን፤ መልካሙን ሁሉ መደገፍ አለብን፣ ለልጆቻችን መልካም ነገር ማውረስ ይገባናል›› ብለዋል፡፡

አገው ምድር በእንግዳ ተቀባይነት የታወቀ፣ ብቻን መብላት የማይወድ ሕዝብ እንደሆነም ነግረውኛል፡፡ ስስት የለም፣ በሰፊው ደግሶ ነው የሚያበለው ነው ያሉት፡፡ የእሳቸውን አይተው ሌሎችም ተሞክሯቸውን እየወሰዱ መሆኑንም ነግረውኛል፡፡ ኢትዮጵያዊ አባትነታቸው ዘንድሮ በሚመረቁት ብቻ እንደማያቃበና ሌሎች ተተኪ ልጆች እንዳሏቸውም ነግረውኛል፡፡ ይሄም ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ ለሦስት ዓመት አባትና ልጅ ሆነው የዘለቁ በርካታ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቁ ነው የነገሩኝ፡፡

ያለፉትን ሦስት ዓመታት ከመልካም አባቱ ጋር የነበረው የዘንድሮ ተመራቂው መስፍን ካሳ ደግነታቸውን ከመገረም በቀር መግለፅ አይቻለም ነው ያለው፡፡ መስፍን ከሚዛን ቴፒ ነው የመጣው፡፡ ሊመረቅ ቀናትን እየጠበቀ ነው፡፡ በእንጅባራ ቆይታው ብዙነህን እንደ ሁለተኛ አባት አድርጎ መልካም ጊዜ እንዳሰላፈ ነግሮኛል፡፡

‹‹ ከጋሽ ብዙነህ ጋር መጀመሪያ ዓመት እንደገባን አካባቢ ነው የተዋወቅነው፣ ቤታቸው ውስጥ ድግስ ነበር፡፡ በመንገድ እየሄዱ ለጓደኞቻቸው ከእኔ ቤት እንዳትቀሩ እያሉ ስልክ ይደውሉላቸዋል፣ በአጋጣሚ እኛ ሰብሰብ ብለን ነበርንና አተኩረን አየናቸው፣ እናንተንም ጠርቻችኋለሁ አሉን፣ ስልካቸውን ሰጡን፣ ደወልንላቸው፣ ከቤታቸው በስርዓት ተቀበሉን፣ በሚገርም ሁኔታ አስተናዱን፣ ከዚያች ቀን ጀምሮ፣ እንደ ሁለተኛ አባት ሆነው ኖርን ፣ በሁሉም ነገር ከጎናችን ናቸው፣ እኔ እንጃ እሳቸውን ለመግለፅ እቸገራለሁ›› ነበር ያለኝ፡፡

ለሌላ ሰው ምሳሌ መሆን የሚችሉ ታላቅ ሰው ናቸው ሲልም ገልጿቿል፡፡ ማኅበረሰቡ ያለው የሰው ፍቅር፣ እንግዳ ተቀባይቱ አስደሳች መሆኑን ነው የተናገረው፡፡ በቆይታዬ በሁሉም ነገር ደስተኛ ነኝ ነው ያለው፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ይሄን መልካም ነገር ማዳበር እንደሚገባቸው ተናግሯል፡፡

እኒህ አባት በአንድ ቤት ውስጥ ኢትዮጵያን ሠሯት፣ ኢትዮጵያዊነትን ኖሩት፣ ፍቅር ሰጥተው ፍቅር ተቀበሉ፣ መልካም አድርገው መልካም ተባሉ፡፡ ዳሩ ለአገው ምድር ፍቅር ነው ማሰሪያው አንድነት ነው ውሉ፤ ኢትዮጵያዊነት ይለምልም።

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post ‹‹ እንግዳ ሲመጣ አገው ምድር ሲደርስ ፣ አዲናስ ይላሉ ቀልብን በሚሰርቁ በሚያማምር ፈረስ።›› appeared first on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 8076

Trending Articles